የዓብይ/የሁዳዴ/የጌታ/ ጾም part 1

የዓብይ/የሁዳዴ/የጌታ/ ጾም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!
ኢዩ 2÷12  “አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ።”
ውድ አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምዕመናንና ምዕመናት እንኳን ለታላቁ የዓብይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡
እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን በአምላካችንንና በመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከታነጸች ጊዜ ጀምሮ የተለያዩና እጅግ ብዙ የሆኑ ጸጋዎችንና ሐብቶችን ለልጆቿ ስታጎናጽፍ ቆይታለች፡፡ ከእነዚህም ታላላቅ ስጦታዎቿ መካከል በየዓመቱ በናፍቆት የምንጠብቃቸው የዓዋጅ ጾሞች ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በዚህ የእውነት ልባዊ መናፈቅ የምንጠብቃቸው የሚሰጡንን የነፍስም የስጋም በረከቶች በማሰብ ነው፡፡
ከላይ በመግቢያችን እንደጠቀስነው እግዚአብሔር በነቢያትን አድሮ ሰው ሁሉ ፍጹም በሆነ የልብ መሰበር፣ መጸጸት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንዲገባው አስተምረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚፈጸመው በጾም በጸሎትና በምጸዋት ነው፡፡ ሰው ከዘላለም ጠባቂያችን እግዚአብሔር መለየት ችሎ ተለይቶ ሳይሆን ኃጢያትን በሰራ ጊዜ ሁሉ ከአምላኩ ጋር ያለውን የረድኤት ግንኙነት በፈቃዱ ያሻክረዋል፣ ያን ጊዜም ከአምላኩ ተለየ ይባላል፡፡ ዘላለማዊ አባቱን የተለየ ሰውም ከእግዚአብሔር እንዲታረቅ ያስፈልጋልና በመጸጸት(ንስሐ በመግባት) ሊጾምና ሊያዝን ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረጋችንም ቀድሞ ለእስራኤል ዘስጋ እንደተነገረ ለእኛ ለእስራኤል ዘነፍሶችም ያስፈልገናልና ጾም የታዘዘው በእግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ከእሱ ጋርም ለመሆን ሁል ጊዜ መጾም ያስፈልጋል፡፡ ለእኛ ለሐዲስ ኪዳን ምዕመናንም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ጾሙን በመጀመርና በመባረክ እኛም እንድንጾም አዝዟል፡፡  
ጾም ማለት በቁሙ ከምግብና ከውሃ ለተወሰነ ጊዜ መከልከል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም አባቶቻችን በሰሩልን ስርዓት መሰረት ማንኛውም ክርስቲያን ከሰባት ዓመቱ ጀምሮ ሁሉንም የዓዋጅ ጾሞች እንዲጾም ታዝዟል፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛው ምዕመን በእውቀት ማነስም ይሁን በሌላ ምክንያት እንደታዘዘው ስርዓቱን ጠብቆ ባይፈጽመውም ቤተክርስቲያን ግን ሁል ጊዜ ታስተምራለች በአባቶቻችን ባርካም ጾሙን ታውጃለች፡፡ ጾም በሁለት ይከፈላል እኚሁም የአዋጅ እና የግል ናቸው፡፡ የአዋጅ የሚባሉትም በቁጥር ሰባት ናቸው፡፡ መለያው ጠባዩም አባቶቻችን ቀድሞ ነቢያት፣ ሐዋርያት እንዳደረጉት የጾሙን መጀመር በቡራኬ፣ በጸሎት፣ በመልካም ምኞትና በምክር ስለሚያበስሩን ነው፡፡ የአዋጅን ጾም ሰው ሁሉ በአንድነት ይጀምረዋል፣ በመመካከር በመረዳዳት ይፈጽመዋል፡፡ የጾሙ መግባትና መውጣትም በሁሉ ለሁሉ የታወቀና የተረዳ ነው፡፡እነዚህም


1.  የነቢያት/የገና/
2.  የገሀድ   
3.  የድህነት /ረቡዕና ዓርብ/
4.  የዓቢይ/የጌታ/
5.  የሐዋርያት/ የሰኔ/
6.  የፍልሰታ/የነሐሴ/
7.  የነነዌ ሰዎች ጾም ናቸው፡፡


በአጠቃላይ ጾም እጅግ በጣም ብዙ ሊባል የሚችል ጥቅም አለው፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
Ø  የኃጢያት ስርየትን እናገኛለን፡፡ ት.ዮናስ 3፡5
Ø  የስጋ በረከትን ያሰጠናል፡፡ ት. ዳን 10፡1
Ø  የሰይጣንን ፈተና እናሸንፍበታለን፡፡ ማቴ 4፡1
በዚህ ወቅት ብንወያይበት ጥሩ የሚሆነው ከየካቲት 9 እስከ ሚያዚያ 4፣ 2007 ዓ.ም ስለሚቆየው ዓብይ ጾም ነው፡፡ የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የብቻዋ የሆነውን የቀን አቆጣጠር ቀመር በመጠቀም እያንዳንዱን ጾም ታውጃለች፡፡
ዓብይ ማለት በአማረኛ ቋንቋ ዋና ማለት ሲሆን ይህም ጾም ዋና ጾም የተባለበት ምክንያት
·         አምላካችንንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመውና የጀመረው በመሆኑ ነው፡፡
·         በጊዜ ርዝመቱ ሰፊው ጾም ስለሆነ ነው፣ 55 ቀን ይጾማልና ነው፡፡
ዓብይ ጾም በቤተክረስቲያናችን የዜማ ሊቅ በሆነው በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት ለእያንዳነዱ ሳምንት ስያሜና የተለየ ስርዓት ተዘጋጅቶለታል፡፡ የሳምንቶቹን ስያሜዎችን በዛሬው ጹሑፋችን ተመልክተን ዝርዝር የሳምንቶቹን መልዕክታት በሚቀጥለው የጽሑፉ ክፍል እናቀርባለን፡፡ እነዚህም የዓብይ ጾም ሳምንቶች በቅደም ተከተል ሲጻፉ እኚህ ናቸው፡፡


1.  ዘወረደ/ ጾመ ሕርቃል/
2.  ቅድስት
3.  ምኩራብ
4.  መጻጉዕ


5.  ደብረ ዘይት/እኩለ ጾም/
6.  ኒቆዲሞስ
7.  ገብር ኄር


8.  ሆሳዕና/ሕማማት ናቸው፡፡



ይህን ጾምም ክርስቶስ እሱ ጾሞ ብቻ ያበቃው ሳይሆን እሱ የቤተክርስቲያን ሙሽራ ከተለያቸው በኋላ ሊጾሙ እንዲገባ አዝዟቸዋል፡፡ማር 2፡19 ሰይጣንን ለማሸነፍም ሁነኛ መሳሪያ እነደሆነ ማር 9፡29 ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አያችልም በማለት አስረግጦ ነግሯቿል፡፡ ሐዋርያትም ቢሆኑ ኢየስሱ ክርስቶስ እናዳዘዘው ስራቸውንም/ ስብከታቸውንም/ ከመጀመራቸው በፊት፣ በአገልግሎታቸውም ወቅት ጾመዋል፡፡ሐዋ 13፡3   

እግዚአብሔር አምላካችን ከጾሙ በረከትና ጸጋ ይስጠን አሜን፡፡

Comments

Unknown said…
a wonder full man will, join the Disciplines' by this fasting as stated above.

Popular posts from this blog

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ የልደት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!!!

በስራው አንተ ያልኩትን ፓትርያርክ መልሼ አንቱ እለው ዘንድ ጸሎቴ ነው፡፡

ይድረስ፤ ለሰማዕታት፣ ለአባቶችና ለቄሳሮቻችን