እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ የልደት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!!!

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
፩ኛ ጢሞ ፩ ፥፲፭ “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ”
ቅዱሳን አባቶቻችን እንደመሰከሩልን የእግዚአብሔር ዓለምን ማዳን ዓለምን ከመፍጠሩ ይደነቃልና ስለዚህ ተወዳጅ እና ሁላችን ተስፋ ስላገኘንበት የጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሚከተሉትን ቁምነገሮች እናገኝበታለን፡፡
v  አምላክ መቼ፣ እንዴትና ለምን ሰው ሆነ›
v  ሰው በመሆኑ ማን ተጠቀመ ማንስ ተጎዳ
v  የሰጠን ድህነትስ እስከምን ድረስ ነው፡፡ በዚህም መሰረት እያንዳንዱን አምላከ ቅዱሳን በረዳን መጠን በዝርዝር እንመልከት፡፡
v  አምላክ መቼ፣ እንዴትና ለምን ሰው ሆነ  ያን ጊዜ በክብር ሳለን በእርሱ እቅፍ ከነሞገሳችን ሆነን የጥንት ጠላታችን ዲያበሎስ ምክንያተ ስሕተት ሆኖ ከክብር፣ ከማዕርግ ና ከሞገሳችን እግዚአብሔር ለይቶ የመከራ ፍድ አመጣብን፡፡ ለሰው ልጅ መሳሳት ሌላ ውጫዊ ምክንያት መዘርዘር አዋጪ እንዳልሆነ በዚያን ጊዜ በተፈፀመው የእውነት ፍርድ ተመልክተናልና፣ ስለዚህም ዛሬም ሆነ ቀድሞ ለስህተታችን የጎላውን ድርሻ መውሰድ ያለብን እኛው እራሳችን ነን ምክንያቱም የተሰጠንን  ኃላፊነት በአግባቡ ስላልተጠቀምንበት ነው እንጂ ክፉ ስራ(ኃጢአት) እኮ ካልነኳት አትነካም፡፡ ሆኖም ግን አክብሮ የፈጠረን እግዚአብሔር ለውርደትና ለሲኦል አልነበረምና አዳም አባታችን በቃረበው አውነተኛ መስዋዕትና ጸሎት የጠብ ግድግዳ የሚፈርስበት የዕዳ ደብዳቤ የሚቀደድበትን እለትና ሁኔታ አመላከተው፡፡ ይህም በመልዕክተኛ ሳይሆን ራሱ “አዳም አዳም ወዴት አለህ” ብሎ ተስፋ በቆረጥንበት፣ መንገድ በጠፋን ጊዜ ቀርቦ ያረጋጋን አምላካችን እግዚአብሔር የአምስት ቀን ተኩል ጊዜ ቀነ ቀጠሮ ተሰጠን፡፡ የዘመኑ(የቀነ ቀጠሮው) መጨረሻ በደረሰ ጊዜም እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደዓለም ላከው፡፡ ገላ 4፡1-6 ዩሐ 1፡ 1-14 ይህም የሆነው ከቅዱሳን ሊቃነ መላዕክት አንዱ በሆነው ቅዱስ ገብርኤል የብስራት ዜና በኋላ ነው፡፡ ያን ጊዜ አይሁድ ቤተመቅደስን ታረክሳለች ብለው በቅናት ካደገችበት ያስወጧት ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁላችን የበሽታችን ፍጹም ፈውስ የሚሆነን ልትወልድልን ቃልን በእምነት ተቀበለች፡፡ የሰራዊትጌታ እግዚአብሔርም ይሁንልኝ ያለችውን ቃል መሰረት አድርጎ ሰው ሊሆን ሰው ሆነ፡፡ ያ የእሱ ያልሆነውን የእኔ ነው ብሎ በትዕቢት ይገዛን የነበረ ሰይጣን መግቢውን ያጣ ዘንድ ክርስቶስ በትህትና አምላክነቱን እንደመቀማት ሳይቆጥር ሰው ሆነ፡፡ ሰው ሲሆንም በመቀላቀል፣ በመለያየት፣ በመጠፋፋት፣ በመለወጥ ሳይሆን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነው በተዓቅቦ ተዋህዶ ነው፡፡ የተጸነሰበት፣ የተወለደበት፣ በግዕዘ ሕጻናት ያደገበት በአጠቃላይ ሰው የሆነበት ምክንያት በሶስት ምድብ ይጠቃለላል፡፡
o   የጥል ግድግዳን ሊያፈርስ፡- ይህ የኃጢያት ክምር የተጠነሰሰው በጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ቢሆንም ይህን ክፉ ውጥን እውን ያደረጉት ግን አዳምና የአዳም የሆነችው እናታችን ሔዋን ናቸው፡፡ ይህን በማድረጋቸው በአንድ አዳም መሳሳት ዓለም ሁሉ ሊወጣበት ወደማይችለውና ወደአልቻለው የሞት ከተማ ገባ፣ በአንድ አዳም ሞት ወደ ዓለም ገባ፡፡ ሮሜ 5፡12 ይህም ሰማይና ምድርን፣ ሰውና እግዚአብሔርን፣ ሰውን መላዕክትን፣ ነፍስና ስጋን የሚያለያይ ክፉ የኃጢያት ውጤት፣ የጠብ ምልክት ግድግዳ ሆኖ ለዘመናት እኚህ ሁሉ ተጣልተው  ይነጉዱ ነበር፡፡ ይህን እኛ የተዘጋጀልንን ክብርና ስጦታ ጥለን ያልተዘጋጀልንን ፍዳና ሞት እንድንቀበል የሚያስገድድ የውል ስምምነት በልቦናቸው ሳይፈቅዱ ይገዙበት ዘንድ አንዱን ግልባጭ በማዕከለ ሲኦል ሌላውን ደግሞ በማዕከለ ዮርዳኖስ አስቀምጦ ጠላታን ይጓደድብን ነበር፡፡ ይህ ሁሉ እውነታኛ ፈራጅ በሆነው አምላካችን ያመጣነው መሆኑን ነቢያት ገልጸዋል ክርስቶስም የቀደመውን ልጅነታችንን፣ ስጦታችንን፣ ጸጋችንን፣ ክብራችንን ይመልስ ዘንድ በጥምቀቱ የዮርዳኖስን በሞቱ የሲኦልን የዕዳ ምስክር ደብዳቤያችንን ቀደደው በዚህም ጥል ተወገደ፡፡ በደሙ መፍሰስ እኛን አነጸን፡፡ ቆላ 2፡!4 ሮሜ5፡9 ራዕ1፡5
o   ለአርዓያ ሰብእ፡- የማናውቀው የእኛ ያልሆነ እንግዳ ምድር ላይ መጥተን መውጫው ሲጠፋን መንገድ ይመራን ዘንድ፤ ወደ እረፍት ስፍራ ያደርሰን ዘንድ ክርስቶስ ሰው ሆነ፡፡ ሰርቶ እያሳየን ፤ እጃችንን ይዞ ከጥምቀት እስከ ትንሳኤ እንዴት እንድንሆን(እንድንመላለስ) አመለከተን፡፡ ተጠምቆ ተጠመቁ፣ አስተምሮ አስተምሩ፣ በጎ ሰርቶ በጎ ስሩ፣ ጸልዮ ጸልዩ፣ ድሃ ረድቶ እርዱ፣ የታመሙትን ፈውሶና ጠይቆ ጠይቁ፣ ዓለምን አሸንፎ አሸንፉ፣ እግር አጥቦ እንዲሁ አድርጉ ብሎ የመንግስተ ሰማይ መንገዱን መራን፡፡ ለዚህ ነው በጎውን ማን ያሳየናል ስንል እሱ ያሳየን፣ ለዚህ ነው ማን ይፈታናል ስንል እሱ ነጻ ያደረገን ይህን ሊያደርግ ተወለደ ሰው ሆነ፡፡ መዝ4፡6 ከፈጸማቸው ሁሉ አብዛኞቹ ለእሱ ለአምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገቡት አልነበሩም ፍቅረ ቀዳማዊ አዳምና ደቂቀ አዳም አገብሮት ዳግማዊ አዳም ቀዳማዊ አዳምን መሰለው ያለጥፋቱ በእሱ ቦታ ተገብቶ ሁሉን ፈጸመ፡፡ 1ኛ ቆሮ 15፡45 ቀዳማዊ አዳም ዳግማዊ አዳምን እያየ እንደቀድሞው የሰማይ አዕዋፋት መርተውት ሱራፊ መልአክ እንደመለሰው ሳይሆን ማንም ሳይቃወመው ተንስኡ ለጸሎት ብሎ ልጆቹን ሰብስቦ እየተከተለ ገነት ገባ ስፍራው(ክብሩ) ደረሰ እንደርስ ዘንድም ስልጣንን ሰጠን ልጅነትን መለሰልን አባ አባት ብለን በልጅነት አንደበት እንድንጠራው አከበረን ጥሪያችንንም በፍጹም አባታዊ ፍቅር ሊሰማን ተስማማ፣ አቤት ውለታው!፡፡ ይህን ሊያደርግ እኛን ሆነ ከክብር አነሰ፡፡
o    ለመድኃኒተ ዓለም፡- ዓለም በአባታችን አዳም ስህተት ታመመች፣ ጎሰቆለች፣ ጎደፈች፣ ደከመች፣ ኩርንችትና እሾህ አበቀለች ይህን በሽታዋን ሊያድን፣ ድካሟን ሊያግዝ፣ ጉስቁልናዋን ሊንድ፣ ጉድፏን ሊሰውር(ሊያነጻ)፣ የማይገባትን ጠባይ ሊያስወግድላት አምላክ ሰው ሆነ፡፡ ዘፍ 3፡18 እሾህ የሰው ልጅ በመበደሉ በየልቦናው የበቀለው የክፋት የኃጢያት አይነቶች ናቸው፡፡ እኚህን ሁሉ ለበሽተኛው ዓለም ጸሐይ እየወጣች ብርሃን ለማይታየው በጨለማ ለተዋጠ ዓለም ብርሃን ይሆን ዘንድ፣ ጎበዝ ሴት ያዘጋጀችው ብዙ ግብዓት ተጠቅማ ልታጣፍጠው ያልቻለችው ወጥን ይመስል የነበረው ዓለም ጨው አግኝቶ ፍጹም ጣፋጭ ጣዕም ልብን የሚያስደስት ጣዕም፣ ዓይንን የሚያስጎመዥ ውበት፣ መዓዛው የሚያውድ ቃና ይሆን ዘንድ ከፍ ከፍ ብሎ ከዛ ቀራንዮ ተራራ ወጥቶ ሰው ሁሉ ከተሰራበት የአፈር አይነት፣ ገነት በምትገኝበት አንጻር፣ የገነት ፈሳሾች ከሚመነጩበት ምንጭ እውነተኛው ኤልሳዕ ክርስቶስ ራሱ ጫው ራሱ ጫው አድራጊ ሆኖ ያች ክርፋታም፣ ህመምተኛ፣ ደካማ፣ ጎስቋላ ና ጨለማ ዓለምን በጣፈጭነቱ አጣፈጣት፣ በመዓዛው አወዳት በቃ አሁን ዓለም የሞት መንደር፣ ለቀስተኞች የሚበዙበት፣ ሙሾ የሚሰማበት መሆኗ ቀረ፡፡ አቤት እውነተኛ መድኃኒት እንዲህ ነው እንጂ በአንድ መድኃኒት መሻር፤ አቤት ባለመድኃኒት እንዲህ ነው እንጂ በአንድ ተግባር ሙሉ ውጤታማነት(ፈውስ መስጠት)፡፡ ይህ እውነተኛ መድኃኒት፣ ጫው፣ ባለመድኃኒት፣ ጨው አድራጊ እሱ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ክርስቶስ ኢየሱስ ዛሬ ተወለደ፡፡ እኛ ይሞቀን ዘንድ እርሱ ብርድ ታግሶ፣ እኛ በነጻነት እነድንኖር እሡ በስደት ፣ እኛ እንድንከብር እሱ ተዋርዶ ሰው ሆነ፡፡   
v  ሰው በመሆኑ ማን ተጠቀመ ማንስ ተጎዳ፡- ተጠቃሚዋች እኛ ብቻ ነን ተጎጂው ደግሞ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ነው፡፡ ይህ ስጋ ለብሶ የረታኝ ማነው ይህስ ሰው መስሎ ከስልታኔ ያዋረደኝ ማነው፡፡ ለዚህ ሁሉ የምከፍለው ባይኖረኝ በጲላጦስ አደባባይ ስላቆምሁ ብቻ ሲኦልን በርብር ነፋሳትን ውሰድ ብሎ በበቃኝ ተረቷልና፡፡ አሾህን በሾህ ይሉሃል እንዲህ ነው ዝቅ ብሎ ከፍ ያሉ መሰላቸውን ማዋረድ ስጋ ለብሶ በእባብ ተሰውሮ እንደረታን በሰፈረው ቁና ተሰፍሮበት ለፍቶ ሰበሰበውን ነፍሳት በኃይሉ ሳይሆን በፍቅሩ ረትቶ ስጋ ለብሶ ሰው ሆኖ ይረከበው ዘንድ ሰው ሆነ፡፡ እኚህን ሁሉ ነፍሳት የሚረከብ ተረክቦም የልባቸውን ደስታ የሚመልስ ከፍጡር ስላልነበረ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ይሆን ዘንድ ንጽሕት ከሆነች ከሴቶች ከተለየች ከቅዱሳን ከከበረች የገሊላ ድንግል ወደሆነች መጥቶ ዛሬ ሰው ሆነ፡፡ ተመስገን!  
v  የሰጠን ድህነትስ እስከምን ድረስ ነው፡- የሰጠን ሕይወትም ሆነ ድህነት እኛ ልንሰራው ያልቻለውን ፍጡር ሊያደርገው የማይችለውን እንጂ የእኛን ስራ ይሰራ ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አልሆነም፡፡ እኛ በእግዚአብሔር ፍቃድ ያቃተን ጽድቅ መስራት፣ እንግዳ መቀበል፣ ትዕግስተኛ መሆን፣ ትንቢት መናገር፣ የዋህ መሆን፣ ለጋስ መሆን፣ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ መመራት(ልበ አምላክ መሆን)፣ ተዓምራት ማድረግ፣ ምልጃ መፈጸም(ስለሌላው መጸለይ)፣ የስጋ ፈውስን ማስቀረት አልነበርም ከዚህ በላይ ልንሞክረው ያልደፈርነው ብንደፍረውም ያልተቻለን ያጣነውን የልጅነት ክብርና ስጦታ ጸጋን ማስመለስ ነበር፡፡ ይህን መማድረግ ከአምላክ በቀር የሚችል ስላልነበረ ሰው ሆነ ሰው በመሆኑም ልጆቹ ሆነናልና ቀድሞ የሰሩት መልካም ስራ ያደረጉት ጽድቅ ተረስቶ ሲኦል ለመግባት እንደተገደዱት ሳይሆን አሁን ነጻ ነን አሁን መዳናችን በእኛ ይወሰናል አሁን የመንግስተ ሰማያት ቁልፋችን በእጃችን ሆኗል፡፡ ስለዚህ የተፈጸመውን የክርስቶስ የዓለምን ይዘን እኛ እያንዳንዳችን እንድን(የቀረውን ድህንት) እንፈጽም ዘንድ አለን(ይገባናል)፡፡ ይህም መዳናችን ከእሱ ስጦታ የተነሳ እንጂ እኛ በቅተን አይደለም፡፡   

ንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ የልደት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!!!


ታህሳስ 28፣ 2008 ዓ.ም

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን

Comments

Popular posts from this blog

በስራው አንተ ያልኩትን ፓትርያርክ መልሼ አንቱ እለው ዘንድ ጸሎቴ ነው፡፡

ይድረስ፤ ለሰማዕታት፣ ለአባቶችና ለቄሳሮቻችን