+እንኳን ለጌታችንና ለመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ልደት በሰላም አደረሳችሁ!!!+


ለሚገባችሁ ና ለሚገባች ጓደኞቼ በሙሉ_____________________________________________
ከዲ.ን መላኩ


1ኛ ዩሐ 4 ÷ 9 “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና፡፡”
ይህ የሆነው እከብር አይል ክቡር፣ እነግስ አይል ንጉስ፣ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ማዕከለ ዓለም ያለና ድህረ ዓለም የሚኖር ሁሉን በፈቃዱ የሚያከናውን የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ በቤተልሔም ሲወለድ ነው፡፡
ከዚህ ፍቅረ እግዚአብሔር መገለጥ በፊት ብዙ አባቶቻችን በምግባር ቢቀኑም ብዙ ነቢያቶችም በትንቢት ቢተጉም ይህን የተከበረ የአምላክ ሰው መሆን ምስጢር በምሳሌና በትንቢት መነጽር አይተውታል እንጂ አልደረሱበትም ፤ ‘’እኛ ግን ዳሰስነው፣ አብረነውም በላን፣ ጠጣን… ይህን የተመለከቱ አይኖቻችሁ፣ ይህን የሰሙ ጆሮዎቻችሁ ብጹዓን ናቸው’’ እንደተባለ፡፡ ይህ የአምላክ ሰው መሆን ልዩ እና ታላቅ ፍቅር ለሰው ልጅ የተገለጠው በእግዚአብሔር በጎ ፍቃድና በሰው ልጆች ሁሉ አባት አዳም ንስሐ መግባት ምክንያት ነበር፡፡ የመገለጡም ዓላማ
v  ኃጢአትን መሻር ዕብ 9÷26 ዩሐ 3÷16
v  የአዳምን የቀደመ ክብሩን መመለስ ገላ 4÷7
v  ለአዳም ልጆች ምሳሌ ሊሆነን ብሎ ዳግማዊ አዳም ከርቀት ወደ ግዝፈት፣ ከምልዑነት ወደ መወሰን መጥቶ የተሰወረ የመለኮትን ነገር አሳወቀን፡፡ ማቴ 3÷16፣
የጨለማ ዘመን ያበቃባት ብርሃን የተገለጠባት ያች የኤፍራታ አውራጃ ቤተልሔምም ቅዱሳን መላዕክትና ሕጻናት በአንድ ቃል የጥል ግድግዳ መፍረሱን በመዝሙራቸው አበሰሩባት፣ እንስሳትና እጽዋትም ያላቸውን ለአምላክ ገበሩባት፣ ምድር ተደሰተች ፋሲካንም አደረገች፡፡ አምላክም በተዋህዶ ከእመቤታችን ከስጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቷልና የሚዳሰስ፣ የሚታይ፣ መከራን የሚቀበል፣ ውሱን ደግሞም ተዓምራትን የሚሰራ፣ ፍጽም ሰው ፍጽም አምላክ ሆነ፡፡ ዩሐ 1÷14፣ 1ኛ ጴጥ4÷1
የመወለዱንም ነገር በቅድምና በስላሴ ኋላም ለአዳም በገባው ቃል ኪዳን የታወቀ ነበርና፤ አባቶቻችን በሱባዔ ሲያመለክቱ ዘመን ሲቆጥሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም ቢሆን እሱ ሰዓት ሳያሳልፍ ቦታ ሳያዛንፍ ዓለም በተፈጠረ 5ሺህ 500 ዘመን በቅዱስ ገብርኤል ብስራት ከድንግል ሰው ሆነ(ተጽነሰ)፡፡ እንደ ሰው ስርዓትም 9ወር ከ5 ቀን በክብርት እመቤትችን ማህጽን ቆየ እንሆ ዛሬ ተወለደ ሰብአ ሰገልም ወርቅ፣ እጣንና ከርቤ እጅ መንሻ አመጡለት ለሕጻኑና ለእናቱም ሰረዱ፡፡ ማቴ 2÷11 መልአክም ምስራች ተናገረ ‘’ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል’’ በማለት፡፡ ሉቃ 2÷8-20
አሁን ዘመኑ የደስታ፣ የምህረት፣ የቅድስና፣ የመዳንና የብርሃን ነው ደስ ይበላችሁ እንድንበት ዘንድ እንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኳልና፣ ደስ ይበላችሁ በጎ የሰራውንና የሚሰራውን ሲኦል መዋጧ ቀርቷልና፣ ደስ ይበላችሁ አገልግሎታችን፣ ድካማችንና ፍቅራችን ከንቱ አይደለምና፣ ደስ ይበላችሁ ለበሽታችን መድኃኒት ተገኝቷል /ተወልዷልና/፡፡

ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ የልደት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!!!

በስራው አንተ ያልኩትን ፓትርያርክ መልሼ አንቱ እለው ዘንድ ጸሎቴ ነው፡፡

ይድረስ፤ ለሰማዕታት፣ ለአባቶችና ለቄሳሮቻችን