በስራው አንተ ያልኩትን ፓትርያርክ መልሼ አንቱ እለው ዘንድ ጸሎቴ ነው፡፡

ጠላት የሆነን (ያዕቆባዊ ኤሳውነት)ፓትርያሪካችን ነው፡፡
እንዴት ቢያነስ ችግራችንን ላለመፈጠሩ ትብብር አለማድረግ ቢያቅተው ችግሩ እንዲፈታ ትብብር አያደርግም፣ እንዴትስ የቅንነት መንፈስ ቢያጥረው የትዕቢትና የበቀል መንፈስ ሰለጠነበት፣ ከዚህ ወዲያ ወድጄ ሳይሆን ተገድጄ አንቱ ማለቴን ትቻለሁ፡፡ ግን በሞቴ ምን አንድነት አለን? ምንም፡፡
እውነት እላለሁ  ማኅበሬ በትክክል ዓለም እንዳልተገባውና ሀገሩም እዚህ አለመሆኑን በተግባር ተረዳሁ፡፡ እሰኪ ማነው የተገፋ? እስኪ ማነው የተናቀው?... እውነት እላለሁ እኔ ዮሴፍን ከሚሸጡ ጋር ዝምድና የለኝም፣ ሕልመኛውን ቀበሮ ጉድጓድ ከሚከቱ በረከት አልሻም፣ ግን ርሃብ ሲመጣ(ሲጸናባቸው) አስጠጋን ማለታቸው አይቀርምና ርሃብ እንደያዛቸው እንዳይሞቱ ሕልሜን ልንገራቸው፡፡
አንተ ዮሴፍ የቤተክርስቲያን ሕልመኛ
          መተዳደሪህ ደንብህን(መኖርህን) የሚጠሉ የበዙብህ
          የአንተ የሆኑት አሳልፈው ሊሰጡህ የሚጓደዱብህ 
          በረከት ፈላጊዎች ግን የሚንከባከቡህ፣ የሚሳሱልህ
          ገና በእስር(በምስረታህ) እያለህ የሚሆኑትን አስቀድመህ የምትናገር
           ተኩላን ለማባረር የአቅምህን የተወጣህ እየተወጣህ ያለህ
.…ሰላም እልሃለው፡፡…ሰላም እልሃለው፡፡.. ሰላም እልሃለው፡፡
አብሬህ ሆኜ እንኳን ትናፍቀኛለህ፣ ከዓይኔ ብሌን ይልቅ ለአንተ ክብር እሰጣለሁ፣ አንተ የምድርን ሳይሆን የሰማይ ብርሃንን ለማየት አብቅተኸኛልና፡፡   
በዘመኔ ስለተገኘህ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፡፡ ዮሴፍ ሆይ ታናሹ ወንድምህ እስኪመጣ ትጠብቃለህ እንጂ የተራቡትን ለመመገብ አስበሃል፣ የደከሙትን ልታጸና አስበሃል፡፡ እኔ አውቃለሁ አንተ ሕልም አለህ፣ አንተ ራዕይ አለህ፣ አንተ ግብ አለህ፣ አንተ እውነተኛ ነህ፣ አንተ ያለአበሳህ ነው የተናቀው፣ ያለጥፋትህ ነው የተሸጥከው፣ ያለስራህም ነው ለቀበሮ ጉድጓድ የተዳረከው….፡፡ አሁን ግን እልሃላው ዮሴፍ ያች ውድዋ እናትህ ስንዱዋ እመቤት በዘረኝነት፣ በአፍቅሮ ነዋይ፣ በአፍቅሮ መንበር … የተተበተቡ ተብትበዋት፤ ቢጠሯት የማትሰማ፣ ቢቀሰቅሷት የማትነሳ፣ መስላለች፡፡ ይህ እኮ የርሃብ ዘመን (የመጣ) ሊመጣ መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ሰው ሲርበው እያየ እናዳላየ እየሰማ እንዳልሰማ መሆን ልማዱ ነው፡፡ ያ እስራኤል(ያዕቆብ)ን ከነልጆቹ ወደ ግብጽ (የፈርኦን ምድረ በዳ) ያሰደደው ርሃብ መጣ፡፡ ያ ርሃብ እኮ የተመረጡትን ወደ አልተመረጡት ያስኮበለለ፣ ተወዳጆችን ለአልተወደዱት ያሰገደ፣ ከበረከት ሀገር ወደ ምድረበዳ ያስኳተነ ርሃብ ነው፡፡ አሁንም ርሃቡ ያዕቆብን ከነልጆቹ(ደጋፊዎቹ) አሰቃይቶታል፣ አሰድዶታል፣ ቤቱን ሰርቶበታል፡፡ አንባቢ ሆይ አስተውል ርሃብ ያልኩህ በቁሙ ርሃብ አይደለም ያማ ምሳሌው ነው አማኑ ይህኛው ነው በኃይሉ ጥቡዕ ነው በብርታቱ ጽኑዕ ርሃብ አሁን ያለው ነው፡፡ ዮሴፍ ሕልመኛውን ብቻ ማግኘት ግድ የሚል የርሃብ ዓይነት ይህ ብቻ ነው፡፡


አንባቢ ሆይ እንዴት ነህ መልዕክቱ ሰመረልህ?፣ ካልሆነ ይስመርልህ ልንገርህ ልቡናህን ሰጥተህ አድምጠኝ      
ዮሴፍ ስደተኛው፣ ሕልመኛው፣ ችግር ጠሪ ተብዬው፣ ያ የሌለ ይናገራል ተብሎ ተከሳሹ፣ አባቶቹን(ንጹሓን መስራቾቹንና መኖሩን ፈላጊዎቹን) አክብሮ ምሳ(ቃለ ወንጌል) በአገልግል(ዓርብ ጉባዔ፣ ግቢጉባዔ፣ አብነት ትምሕርት፣ ዐውደ ርዕይ፣ ሐዊረ ሕይወት…) አድርገህ አድርስ ተብሎ በቅን አባቶቹ ታዞ ሊያደርስ የሄደው በመሄድ ላይ ያለው… ፤ በማድረሱም፣ በመድረሱም፣ በመታዘዙም ክፉ የደረሰበት፣ ክፉ የተመከረበት፣ የተዛተበት(ሃራ ጥቃ፣ ፓትርያርክ)፣….. ማኅበሬ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡
ያዕቆብ ልጁን ወደልጆቹ የላከ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ የኋላ ኋላ ግን ይሳቅን የእሱ(ጸጉረ ኤሳው) ያልሆነውን ለብሶ እንዳታለለ ዛሬም የፈቀዱትን ሳይሆንና ሳይመስል ምሳ ሊያደርስ የተላከውን የሚያንገላታ ርሃብተኛ አባት ያዕቆብ ይህ ነው፡፡ ልብ በል አንባቢ ርሃብ ልዩ ነው የምግብ የምልህ አይደለውም እሱንማ…. በወርቅ ሳሕንና መጠጫ… ቀርቦለት የለምን፡፡ ምነው እመብርሃን ያዕቆብ ያዕቆብነቱን ለቆ ታላቅ ውሸት፣ ውርደት፣ ዝቅተት፣ ንቀትና ርሃብ ሲገባ ዝም አልሽው አንቺ ለኢትዮጵያ ተስፋ ነሽ እኮ አንቺ ለያዕቆብ ተስፋ እንዳይቆርጥ መሰላሉ ነበርሽ እኮ…. ተይ ርሃቡን በቃህ በይው ያዕቆብ በስተርጅናው ወደ ሃሩር በርሃ(ሲኦል) ሲሰደድ ዝም አትበይው፡፡ ልቡናውን መልሽ ከልጅሽ አስታርቂው ከልጆቹ ይታረቅ ዘንድ፡፡
የበረከት ሀገር  ያልኩህ እናቴን ….. እምዬን ነው፡፡ እሷማ ያለስሟ ስም ተሰጣት፣ ያለግብሯ ግብር ወጣላት… የርሃብ ምድር ተሰኘች ምክንያቱም ዮሴፍን ላኪው ያዕቆብ በመሪ(ታላቅ አባት) ተብዬው አማካይነት ጸጉር ለብሶ መመረጡን ረስቶ ካቶሊክና ተዋህዶን መለየት አቅቶት፣ የራሱ እያረረበት የሰውን ያማስል ዘንድ ያለአባቶች ፍቃድ ቫቲካን ሮም በሄደው ያዕቆባው ኤሳው ምክንያት ነው፡፡
ግብጽ ያልኩህ በቁሙ አይደለም ይህማ እንዴት ይሆናል ካልከኝ ስማኝ ላዋይህ፡፡ ሃሩር በግብጽ አለ፣ አለመመረጥ በግብጽ ነበረ፣ ጣኦት በግብጽ ነበር…. እናም እልሃለው ከአቡነ ተክለሃይማኖት መንበር ከተመረጠው ይልቅ ወደ አልተመረጠው የፍራንሲስ ጠቅላይ ግዛት ያልታደለው(ኤሳው መሳይ ያዕቆብ) ሄደ፡፡ አንድም በዚህ ዋዕይ እንዳለ አምሳሉ ወደሆነችው ሲኦል ፓትርያርኩ ጉዞ ጀመረ፡፡ ምክንያቱም ያዕቅብነቱን ዘንግቷልና፡፡



ርሃብ ያልኩህ ያው ማጣት ነው ግን የታጣው ነገር ልዩ ነው፡፡
ርሃቡ የዕውቀት ነው
ርሃቡ የቅድስና ነው
ርሃቡ ክብርን ያለመጠበቅ ነው
ርሃቡ የልጆችን ጸባይ አለማወቅ ነው
ርሃቡ እኔ ብቻ አውቃለሁ ማለት ነው
ርሃቡ ጸሎት፣ ጾም፣ ስግደት ነው
ርሃቡ የፍቅር ርሃብ ነው
ርሃቡ የእምነት ነው
ርሃቡ የአብነት መምሕራንን አለማክበር ነው
ርሃቡ የእውነት ርሃብ ነው…..
ምን  እላለሁ ዮሴፍ የርሃቡን ዓይነት ቀድመህ አውቀህ ጥቂትም ቢሆን ተዘጋጅተሃልና አሁንም ያዕቅብ ያዕቆብነቱን ዘንግቶ ተርቦ መጥቷል ተቀበለው አስጠጋው… አንተም ብትሆን ርሃብ እንዳገባህ በርታ ተስፋይቱን ምድር በእስርም፣ በጲጥፋራ ቤትም፣ አስተዳዳሪነትም ብትሆን ሆነህ አትርሳ፡፡ አንባቢ ሆይ ብዙ የተራብን ተመግበንበታልና እየተመገብንበት ነውና ማኅበረ ቅዱሳን ርሃብን እንዲጠፋ የቻልከውን አግዝ፡፡ ይህን ባታደርክ እምዬ ማርያምን እልሃለው የአባቶችህ(የመስራቾቹ) አጥንት አንተን ይወጋሃል፡፡
የራበን እንበላበት ዘንድ ቀረበ የአንድነት ማዕድ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡ የተራቡትን እንመግብበት የተሰራ አዳርሽ(ግብር ቤት)፣ ሰቀላ ማኅበረ ቅዱሳን ነው፡፡
ለእኔ ግን ‘’ማኅበረ ቅዱሳን በእውነትም ማኅበረ ቅዱሳንን ሆኖልኛል’’፡፡
በስራው አንተ ያልኩትን ፓትርያርክ መልሼ አንቱ እለው ዘንድ ጸሎቴ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሆይ የግብጽን ቤተክርስቲያን እንደሰማህ እኛንም ስማን፣ ሰው ሆነ መሪ ስጠን!!!

ይቆየን፡፡

Comments

Popular posts from this blog

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ የልደት በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!!!

ይድረስ፤ ለሰማዕታት፣ ለአባቶችና ለቄሳሮቻችን