የዓብይ/የሁዳዴ/የጌታ/ ጾም part 1
የዓብይ/የሁዳዴ/የጌታ/ ጾም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን! ኢዩ 2÷12 “አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ።” ውድ አባቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምዕመናንና ምዕመናት እንኳን ለታላቁ የዓብይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡ እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን በአምላካችንንና በመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከታነጸች ጊዜ ጀምሮ የተለያዩና እጅግ ብዙ የሆኑ ጸጋዎችንና ሐብቶችን ለልጆቿ ስታጎናጽፍ ቆይታለች፡፡ ከእነዚህም ታላላቅ ስጦታዎቿ መካከል በየዓመቱ በናፍቆት የምንጠብቃቸው የዓዋጅ ጾሞች ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በዚህ የእውነት ልባዊ መናፈቅ የምንጠብቃቸው የሚሰጡንን የነፍስም የስጋም በረከቶች በማሰብ ነው፡፡ ከላይ በመግቢያችን እንደጠቀስነው እግዚአብሔር በነቢያትን አድሮ ሰው ሁሉ ፍጹም በሆነ የልብ መሰበር፣ መጸጸት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንዲገባው አስተምረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚፈጸመው በጾም በጸሎትና በምጸዋት ነው፡፡ ሰው ከዘላለም ጠባቂያችን እግዚአብሔር መለየት ችሎ ተለይቶ ሳይሆን ኃጢያትን በሰራ ጊዜ ሁሉ ከአምላኩ ጋር ያለውን የረድኤት ግንኙነት በፈቃዱ ያሻክረዋል፣ ያን ጊዜም ከአምላኩ ተለየ ይባላል፡፡ ዘላለማዊ አባቱን የተለየ ሰውም ከእግዚአብሔር እንዲታረቅ ያስፈልጋልና በመጸጸት(ንስሐ በመግባት) ሊጾምና ሊያዝን ይገባዋል፡፡ ይህን ማድረጋችንም ቀድሞ ለእስራኤል ዘስጋ እንደተነገረ ለእኛ ለእስራኤል ዘነፍሶችም ያስፈልገናልና ጾም የታዘዘው በእግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ከእሱ ጋርም ለመሆን ሁል ጊዜ መጾም ያስፈልጋል፡፡ ለእኛ ለሐዲስ ኪዳን ምዕመናንም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ጾሙን በመጀመርና በመባረክ እኛም እን...